.

ሐሰተኛ ማሰረጃ

ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሠለፍ በሁሉም አቅጣጫ እንቅስቃሴ ከጀመረች ውሎ አድሯል፡፡ ህብረተሰቡና መንግስት እጅለእጅ ተያይዘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሀገራችን ስሟ በምሳሌነት በምትጠራበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህ ለተመዘገበው ውጤት ደግሞ በአሁን ጊዜ ያለው አስተማማኝ ሠላም ከፍተኛ ቦታ አለው፤ ለምን ቢባል በሠላም ወጥቶ በሠላም ለመመለስ፣ የፈለጉትን ሰርቶ እራስም ተለውጦ ሀገርም የተፈለገው የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሳ ለማየት ከሠላም ሌላ የማይታሰብ በመሆኑ ነው፡፡ስለዚህ የተጀመረው እንቅስቃሴ ያለ አንዳች ችግር እንዲቀጥል ወንጀሎችና የሰላም ስጋትና እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡ የሠላም ስጋት ከሆኑ ወንጀሎች መካከል የሐሰት ማስረጃ አንዱ ነው፡፡የሐሰት ማስረጃ እውነትን በማዛባት ያልተገባ ፍትሕ ወይም ሌላ ሰው እንዲያገኝ ከመርዳት የሚመነጭ ነው፡፡ይህ ደግሞ ወንጀል የሰራን ሰው ነፃ ለማውጣት ወይም ከወንጀል ነፃ የሆነን  ሰው በወንጀል እንዲጠየቅ ማድረግንም ይጨምራል፡፡

የሐሰት ማስረጃ በተያየ መልክ ሊቅርብ ይችላል፡፡የሐሰት ማስረጃ የሐሰት የቃል ምስክርነትና የፅሑፍ መረጃ ሊሆን ይችላል፡፡የሐሰት ማስረጃ ግለሰቦች ለፖሊስ፣ ለአቃቤ ህግና በፍርድ ቤት ወይም በሌላ ቦታዎች በመቅረብ በጥቅም ወይም በዝምድና ግንኙነት አንደኛውን ጠቅሞ ሌላኛውን ለመጉዳት የሐሰት ምስክርነትና እውነት ያልሆነ ቃል በህግ ፊት በመስጠት የሚፈፀም ወንጀል ነው፡፡ተቀነባብሮ ለፍትሕና ለደህንነት አካላት በሚቀርብ የሐሰት ማሰረጃ ብዙ ሰዎች ያለ ድርጊታቸው ፀባይ ማረሚያ እንዲገቡ ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡

ሌላኛው የወንጀል ድርጊት በፅሑፍ የሚዘጋጅ የሐሰት ማስረጃ ወንጀል ነው፡፡ የሐሰት የጽሑፍ ማስረጃ ማዘጋጀት ወንጀልና በነዚህ ማስረጃዎች መጠቀም እንደ ክልላችንም ሆነ እንደ ሀገር  በብዛት እየታየ ስለሆነ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተላያየ ቦታዎች አንዳንድ የፖሊስ ማስረጃዎች በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሚያሳዩት አንዳደንድ ወንጀለኞች የመስሪያ ቤቶችን ማህተም፣ የባለስልጣንን ፊርማና ቲተር አስመስሎ በመስራት በሐሰት የትምህርት ማስረጃዎች ለመቀጠር ወይም ለማደግ መሞከር፣ የሐሰት መንጃ ፍቃድ ማዘጋጀትና መጠቀም፣ የሐሰት የሞያ ብቃት ማረጋገጫ በማቅረብ ለመወዳደር መቅረብ፣ የሐሰት ፓስፖርት ማዘጋጀት በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት መሞከር ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች ከህግ ሳይሰወሩ ተይዘው በህግ ፊት ቀርበው ተቀጥተዋል፡፡

የሐሰት ማስረጃ ተጠቅሞ ፍትሕን ማጣመም፣ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን፣ ጥገኝነትና ሙሰኝነት እንዲስፋፋ መንገድ የሚከፍት ከመሆኑም ባሻገር በስነምግባር ጠንካራ የሆነ፣ ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር እንቅፋት የሆነ በራስ መተማመን በማሳጣት ያንድን የሞያ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ወንጀል ለህግ የበላይነት እንቅፋት የሆነና የሰዎችን ሰብዓዊ መብት የሚገፋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ስለዚህ ይህ በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ መልክ የሚፈፀም የሐሰት ማስረጃ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅህኖ ቀላል ስላልሆነ ማንኛውም ዜጋ የዚህን ወንጀል ድርጊት በማውገዝ መከላከል አለበት፡፡ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ግንዛቤ ለማጠናከር መስራት አለበት እንላለን፡፡

Go to top