የማህበረሰብ የፖሊስ አገልግሎት
የማህበረሰብ የፖሊስ አገልግሎት
ከ1980 በፊት በነበረው ትምህርት ውስጥ በተለይ በሰሜን አሜሪካ ወንጀል በእጅጉ እየተስፋፋ ከምጣቱም በላይ የህብረተሰብ ችግርና ብጥብጥ እየከፋ መጣ፡፡ በዚያን ጊዜ በዘልማዳዊ አሠራር ውስጥ የነበረው የፖሊስ ኃይል እነዚህን ችግሮች ብቻውን መቆጣጠርና መፍታት እንዳልቻለ በተጨባጭ ግልፅ እየሆነ ስለመጣ በ1980ዎቹ አዲሱ የፖሊስ አገልግሎት ሐሳብና ዘዴ ሥራ ላይ እንደዋለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ አዲሱ የፖሊስ አገልግሎትም ‘የማህበረሰብ ፖሊስነት’ ወይም ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ የሚባለው ነው፡፡የዚህ ሐሳብ መነሻ ማንኛውም የፖሊስ ስራ በተለይም የወንጀል መከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ ከሌለው ሥኬታማ ሆኖ ከግብ ሊደርስ እንደማይቻል ከግንዛቤ ላይ በመደረሱ ነው፡፡
ይህ ፍልስፍናም በግንባር ቀደምነት በሶስት ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡እነሱም፡- አብሮ መስራት (Partineship)፣ ችግር መፍታት(Problem solving) እና ለውጥ ወይም የድርጅት ሽግግር/Institutional Transformation/ ሲሆን ይህ አሰራር ተግባራዊ መሆን በጀመረባቸው አከባቢና ሀገሮች ውጤታማ እየሆነ ስለመጣ በዛሬ ጊዜ በብዙ የዓለም ሀገራት ውስጥ በስፋት ስራ ላይ እየዋለ ነው፡፡
የማህበረሰብ ፖሊስነት ወደ ሀገራችን መጥቶ የፖሊስ ተቋም አጀንዳ መሆን የጀመረው በ1989 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ የፖሊስ ተቋምን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግርና ወቅታዊ አማራጭ የሆነ ፍልስፍና በዚያን ጊዜ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ግንዛቤው ስላለነበረ ውጤቱ የተለያየ መልክ የያዘ ከመሆኑ የተነሳ እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ ውጤት ሳያስመዘግብ ቆይቷል፡፡
የማህበረሰብ ፖሊስ ፍልስፍና በሀገራችን በተጨባጭ ሁኔታ ስራ ላይ በዋለ ጊዜ ይህን ፍልስፍና ቀድመው ስራ ላይ ካዋሉ ጥቂት ክልሎች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ቁልፍ የሰላም ስራ በትኩረት ታይቶ ወደ ተግባር ለመለወጥ ግንዛቤው ስላልተስፋፋ የፍልስፍናው አሰራር በተፈለገው ደረጃ ስራ ላይ ውሏል ለማለት አይቻልም፡፡ ባለፉት አስርተ ዓመታት ሲሰጥ የነበረው የወንጀል መከላከል ትምህርት በማህበረሰብ ፖሊስ መርሆች ላይ የተመሰረተ አልነበረመ፡፡ የወንጀል መከላከል ትምህርቱ የተሰጣቸውን ግለሰቦች ብዛት ከመቁጠር ያለፈ በተሰጠው ትምህርት የተገኘውን ለውጥና ውጤት እየመዘነ የሚሄድ አልነበረም፡፡ ባጠቃላይ ሲሰጥ የነበረው የወንጀል መከላከል ግንዛቤ በማህበረሰብ ፖሊስን የሚያንፀባርቅና የህበረተሰቡን ተሳትፎ የሚያበረታታ አልነበረም ለማለት ይቻላል፡፡
ከጊዜ በኋላ የማህበረሰብ ፖሊስ አሰራር አስፈላጊነት እየጨመረ ስለመጣ ከ2002ዓ.ም ጀምሮ በማህበረሰብ ፖሊስ ሞያ የሚሰለጠኑ አመራሮችን በቀበሌ ደረጃ በመመደብ ፍልስፍናው ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲስፋፋ መደረግ ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ የማህበረሰብ ፖሊስ ስራ በክልሉ ህብረተሰብ ውስጥ በተጨባጭ ውጤታማ ለውጥ መምጣት ጀምሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከክል እስከ ቀበሌ ያሉ የፖሊስ መዋቅር ተዘርግቶ ቁጥራቸው ይህ ነው የማይባል የማህበረሰብ ፖሊስ አመራር ህብረተሰቡ ውስጥ ተመድበው ቀላል የማይባል ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ይህ በክልሉ ውስጥ የሚታየው የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ስራ በጥናት የተደገፈ ስትራቴጂ፣ደንብ፣ መመሪያና ማኑዋል ስላልሆነ ሲሰራ የነበረው ስራም ወጥነቱ የተረጋገጠ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ከተሞችና ቀበሌዎች ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ልዩነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡
አሰራሩን በክልላችን ተጨባጭ ሁነታ ስራ ላይ ማዋል ላይ የሚታየው የአመራርና የአባላት ፖሊስ የግንዛቤና ቆራጥነት ማነስ ከነበሩት ችግሮች ከፍተኞቹ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት ለዚህ ስራ ይሰጥ የነበረውና ያለው አመለካከት ደካማ ነው፡፡ የማህበረሰብ ፖሊስ አመራሮች ለሌላ ስራ ቅድሚያ መስጠት፣ አልፎ አልፎ ብቃት የሌላቸው አባላትን መመደብና አንዳንድ የፖሊስ አባላትም ይህን ስራ እንደ አንድ አብይ ስራ ተመልክቶ በቆራጥነት ከመስራት ይልቅ ሌሎች የፖሊስ ስራዎችን መምረጥ የነበሩ የአመለካከትና ከነበሩ የግንዛቤ ችግሮች ውስጥ ይቆጠራሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረው ትኩረትና ቆራጥነት በተለያዩ ደረጀዎች የሚገኙ አመራሮች ዘንድም ተመሳሳይ ስላልነበር ሊደረስበት ከታሰበው ግብ አንፃር ሲመዛዘን ብዙ የሚቀረው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ እነዚህንና የመሳሰሉትን ችግሮች በመፍታት የማህበረሰብ ፖሊስ አሰራር በሚፈለገው ደረጃ ከህብረተሰቡ ደርሶ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ አሰራሩ የሚመራበትን ስትራቴጂና መመሪያ እያዘጋጀ ሲሆን ወደፊት በሁሉም ደረጃ ያሉ አመራሮችና አባላት ግንዛቤ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ሰፊው ህብረተሰብ ግንዛቤ እነዲያገኙ የግንዛቤ ማሰጨበጫ ስራ በሁሉም ቦታ ይደረጋል፡፡
’አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ሠላም በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አቅጣጫ አብረን እናረጋግጥ’ !
|
|
|
ይከተሉን
|
Copyright © የኦሮሚያ ፖሊስ ኮምሽን 2023. መብቱበ ህግ የተጠበቀ ስልክ. 011-4164044 |
||
